ከአማራ ተወላጆች እና የአማራ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኢትዮጵያውያን ጋር የተደረጉ ምክክሮች ስኬታማ እንደሆኑ የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አስታወቁ፡፡

የሥራ ኃላፊዎቹ በሰሜን አሜሪካ ግዛቶች ከሕዝብ ጋር ሲያካሂዷቸው የነበሩትን ምክክሮች አስመልክተው ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና በአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታ የተመራ የአማራ ክልል የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ በሰሜን አሜሪካ-ዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው፣ አትላንታ፣ ዴንቨር፣ ኮሎምበስ፣ ሚኒሶታ፣ ሳንሆዜ እና ሲያትል ከሚኖሩ የአማራ ተወላጆች እና የአማራ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኢትዮጵዉያን ጋር ሲመክር መሰንበቱ ይታወሳል፡፡ ምክክሩ በክልላዊ እና ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች፣ በክልሉ ልማት እና ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ የአልማን የቀጣይ ሦስት ዓመታት የለውጥ ዕቅድ ዕውን ለማድረግ እና ዓላማውን በዘላቂነት ለመደገፍ የዳያስፖራው ሚና ምን መሆን እንዳለበትም በምክክሩ ትኩረት ተደርጓል፡፡ ከተሳታፊዎችም በሁሉም ዘርፎች ጥያቄ እና ምክረ ሀሳቦች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል፡፡

የአልማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታ እንደተናገሩት ምክክሩ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች ግልጽ መረጃ ኖሯቸው በክልላቸው እና በሀገራቸው ልማት ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችል ነበር፡፡

ጥቃቅን ልዩነቶችን በመተው የጋራ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በተቀናጀ መልኩ ለመሥራት፣ የክልሉን እና የሕዝቡን ኅልውና በማስጠበቅ እንዲሁም ኢኮኖሚውን በማሻሻል ላይ ከንግግር ያለፈ ተግባር ለመፈጸም መወያዬታቸውን፣ ይህንም ዕውን ለማድረግም በውይይቶቹ ስምምነት ላይ መደረሱን አቶ መላኩ አስረድተዋል፡፡

አልማን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመደገፍ እና ለማጠናከርም በየግዛቶቹ አደረጃጀቶች ተፈጥረዋል፤ ዋሽንግተን ዲሲ ላይም ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል አደረጃጀት እንደሚኖር አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ መላኩ ማብራሪያ ጉዞውም የተሳካ፣ መግባባት እና መቀራረብ የተፈጠረበት፣ ለአንድ ዓላማ በአንድነት መቆም እንደሚገባም ስምምነት ላይ የተደረሰበት ነው፡፡

ከጋዜጠኞችም የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ፣ በውጭ ሀገራት ያሉ የአማራ ተወላጅ ምሁራንን አቅም አሰባስቦ ለመጠቀም ምን እንደታሰበ እና ምቹ የኢንቨስትመንት አሰራር በክልሉ እንዲኖር ለማድረግ ምን እየተሰራ እንደሆነ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ ቧያለው በሰጡት ማብራሪያም በአሁኑ ወቅት አማራ ክልል ውስጥ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱንና ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ምሁራን መማክርት እያደረገ ያለውን አወንታዊ እንቅስቃሴ ያደነቁት አቶ ዮሐንስ በውጭ ሀገራት የሚኖሩት ምሁራንን ምቹ አሰራር በመፍጠር አቅማቸውን ለመጠቀም እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡ በእረፍት ጊዜያቸው እና በተለያዩ አጋጣሚዎች አሁንም ለክልሉ እና ለሀገራቸው ድጋፍ እያደረጉ ያሉ መኖራቸውንም ነው የተናገሩት፡፡ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ደግሞ በአገልግሎት አሰጣጥ እና በሀይል አቅርቦት የሚስተዋሉ ችግሮችን በማስተካከል የክልሉን የኢንቨስትመንት አቅም ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ነው ያስገነዘቡት፡፡

በሁሉም አካባቢዎች በተካሄዱት ውይይቶች ነዋሪዎቹ እና የአማራ ወጣቶች ማኅበራት በክልሉ ሰባት የዳስ ትምህርት ቤቶችን ደረጃቸውን ጠብቀው ለማሰራት ቃል መግባታቸውን አብመድ ተመልክቷል፡፡ በውይይቱ የተሳተፉ ወገኖችም ለአልማ ድጋፍ በዓመት ከተጠየቀው 120 ዶላር በላይ ለመክፈል፣ በአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር እና በሌሎችም ልማቶች በገንዘብም ሆነ በሙያቸው ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎቱ እንዳላቸው አብመድ ዘግቧል፡፡


Copyright © 2012  ADA, All Rights Reserved.               Designed & Developed by :Yibeltal Ferede